ቤት አልሚዎችን ከገዢዎች የሚያገናኘው የሪል ስቴት ኤክስፖ ተከፈተ


"ይህንን ሳያዩ ቤት እንዳይገዙ" በሚል መሪ ቃል  ከዛሬ የካቲት 16 እስከ ማክሰኞ የካቲት 19 2016 ዓ.ም በሚሊኒየም አዳራሽ የሚካሄድ መሆኑን አርኪ የሪል ስቴት ኤክስፖ አዘጋጅ አስታውቋል። የአርኪ ሆምስ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ቢኒያም ግርማ ለብስራት ሬድዮና ቴሌቪዥን እንደተናገሩት በቤት ግንባታ ዘርፍ የተሰማሩ ባለሀብቶች ከቴክኖሎጂ አሰራር ስርዓትና ፕሮጀክት ውጤታማነት አንጻር እርስ በርስ  ልምድና ልውውጥ የሚያደርጉበት ኤክስፖ ነው ብለዋል። ይህንን ኤክስፖ 10ሺ ሰዎች ይጎበኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።በኤክስፖ ላይ  ቤቶቹን በማቅረብ የሪል ስቴት አልሚዎች ሲሳተፉ በፋይናንሱ በኩል ደግሞ ባንኮችም ተሳትፎ የሚያደርጉበት ነው ።ኢንቴርየር ዲዛይን (ቤት የማስዋብ አገልግሎት)ላይ የተሰማሩ  እና የእንጨት ስራ ውጤቶችን የሚያቀርቡ ፈርኒቸር  ቤቶችም በኤክስፖው ላይ ተሳታፊ ሆነዋል። ኤክስፖው ሁሉም በአንድ ቦታ በማካተት ቤት መግዛት ለሚፈልገው ማህበረሰን ዋጋን ጥራትንና ሌሎችንም መረጃዎችን ለማሰባሰብ የሚያባክነውን ጊዜና ጉልበት የሚቆጥብ ነው፡፡ የሪል ስቴት ዘርፉ በቴክኖሎጂ እንዲታገዝ በቴክኖሎጂ ስራ ላይ የተሰማሩ ድርጅቶች የቤት አስተዳደር ስርዓትን ከማቅለል አንፃር የሚጫወቱት ሚና ጉልህ እንደሆነ ተጠቁሟል።እንዲህ አይነቱን ኤክስፖ በርካታ ሃገራት ከቤት ግብይት አንጻር እንደ አንድ ኢኮኖሚ ማንቀሳቀሻ ቢጠቀሙበትም በኢትዮጵያ ግን ብዙም የተለመደ አይደለም። አርኪ ኢቨንት ኦርጋናይዘር ለሁለተኛ ጊዜ የሪልስቴት ኤክስፖን አዘጋጅቷል።